Read Online in Amharic
Table of Content
መግቢያ እና ይዘቶች
መሰረታዊ መረጃ
የኩላሊት መድከም
ሌሎች ዋና ዋና የኩላሊት ህመሞች
የኩላሊት ህመም ወቅት አመጋገብ

19. የኩላሊት ጠጠር ህመም

የጠጠር ህመም በብዛት ከሚከስቱ ህመሞች መካከል አንዱ ነው። የኩላሊት ጠጠር በአብዛኛው በጣም ከፍተኛ ህመም የሚፈጠር ህመም ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ምንም አይነት ምልክት ላያሳይ ይችላል። የጠጠር ህመም የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሊፈጥርና የኩላሊትን ስራ ሊያውክ ይችላል። ስለዚህም የመከላከያና የህክምና መንገዶችን ማወቅ ተገቢ ነው።

የኩላሊት ጠጠር ምንድን ነው?

የኩላሊት ጠጠር ጠንካራ የሆነ በኩላሊት ወይም በሽንት ማስተላለፊያ አካላት ውስጥ የሚፈጠር ጠጠር ነው። በሽንት ውስጥ የጠጣር ነገሮች ወይም እንደ ካልሲያም ኦክሳሌት፣ ዩሬት ወይም ፎስፌት ያሉ ቅንጣቶች መብዛት ምክኒያት እንደሆነ ይታመናል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቅንጣቶች በሽንት ውስጥ ተከማችተው ቀስ በቀስ በመጠን ከጨመሩ በኋላ በረጅም ጊዜ ጠጠር ይፈጥራሉ።

ምንም አይነት እክልበማይኖርበት ጊዜሽንት ውስጥ ቅንጣቶች እንዳይሠባሠቡ የሚያደርጉ ንጥረ ነገሮች አሉ። የነዚህ ንጥረ ነገሮች መዛባት በኩላሊት ጠጠር መፈጠር አስተዋፅዖ ያደርጋል። የሽንት ማስተላለፊያ አካላት ውስጥ የሚፈጠር የጠጠር ህመም የሀሞት ከረጢት ውስጥ ከሚከስተው የሀሞት ጠጠር የሚባለው ህመም የተለየ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

የሽንት ማስተላለፊያ ጠጠሮች ምን አይነት መጠን ፣ ቅርፅና ቦታ ይኖራቸዋል?

ጠጠሮች በመጠንና ቅርፅ ይለያያሉ። መጠናቸው ከአንዲት ፍሬ አሸዋ እስከ ቴኒስ መጫወቻ ኳስ ሊለያይ ይችላል። ቅርጻቸውም ለስላሳ ገጽ ያላቸው ድቡልቡልና ሞላላ ሊሆን እንደሚችሉ ሁሉ በጣም ሻካራና በወል የማይታወቅ ቅርፅ ያላቸው ሊሆን ይችላል። ለስላሳ ገፅ ያላቸው ጠጠሮች የሚፈጥሩትህመም ቀነስ ያለና ለመወገድ ብዙ የማያስቸግሩ ናቸው። በአንፃሩ ሻካራ ጠጠሮች የሚፈጥሩት ህመም ከፍተኛ ሲሆን በቀላሉ መወገድ የማይችሉ ናቸዉ። ጠጠር በየትኛውም የሽንት ማስተላለፊያ አካል ውስጥ ሊከሰት ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ በኩላሊት ተፈጥሮ ወደላይኛው የሽንት ቧንቧ (ዩሬተር) አልፎ ጠባቡ ቦታ ላይ ይቀረቀራል።

የኩላሊት ጠጠር አይነቶች

አራት ዋና ዋና የኩላሊት ጠጠር አይነቶች አሉ:

1.   ካልሲያም ጠጠሮች: 70-80% የሚገኘው የጠጠር አይነት ይሄ ሲሆን የሚሰራው ካልሲየም አክሳሊት ወይም ካልሲያም ፎስፌት የሚባሉ ውህዶች ነው። ካልሲየም ኦክሳሌት ጠጠሮች ጠንካራና ለማሟሟት የሚከብዱ ሲሆን ካልሲየም ፎስፌት ጠጠሮች በቤዝ ሽንት ውስጥ የሚገኝ ነው።

2.  ስትሩቫይት ጠጠሮች፡ ከማግኒዚየም አሞኒየም ፎስፌት የሚሰሩ ሲሆን 10-15 በመቶ የሚሆኑ የጠጠር ህመሞች ላይ የሚገኙ ናቸው። ይህ የጠጠር አይነት ሴቶች ላይ የሚገኝ ሲሆን በቤዝ ሽንት ላይ የሚፈጠር ው።

3.  ዩሪክ አሲድ ጠጠር፡ ይህ የጠጠር አይነት ከ 5–10 በመቶ የሚሆኑ የጠጠር ህሙማን ላይ የሚገኝ ሲሆን አሲዳማ የሆነና በውስጡ ብዙ ዩሪክ አሲድ ያለው ሽንት ላይ የሚፈጠር ነው።

ይህ የጠጠር አይነት ሪህ ያለባቸው ፣ የእንስሳት ተዋፅኦ አብዝተው የሚመገቡና የካንሰር መድሀኒት የወሰዱና ሰውነታቸው ዉስጥ በቂ ውሃ የሌለ ሰዎች ላይ የሚፈጠር ነው። ዩሪክ አሲድ ጠጠር በራጅ ለማግኘት ከባድ ነው።

4.  ሲስቲን ጠጠር: ይህ የጠጠር አይነት ሲስቲንዩሪያ የተባለ በወላጆች የሚወረስ ህመም ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ነው። ሲስቲንዩሪያ በሽንት ውስጥ ከፍተኛ የሲስቲን መጠን በመኖሩ የታወቀ ነው።

ስታግሆርን ጠጠር ምንድን ነዉ?

ስታግሆርን ጠጠር በጣም ትልቅ ስትሩቫይት ጠጠር ሲሆን የኩላሊት አብዛኛው ክፍል ላይ ስለሚቀመጥ የአጋዘን ቀንድ ይመስላል። ስታግሆርን በኢንግሊዘኛ የአጋዘን ቀንድ ቅርፅ ማለት ነው። ይህ የጠጠር አይነት በጣም ትንሽ ወይም ምንም አይነት ህመም የማይፈጥር ሲሆን በዚህም ምክኒያት ምርመራ ለማድረግ ጊዜ ስለሚወስድ ኩላሊትን ሊጎዳ ይችላል።

ኩላሊት ጠጠር እንዲፈጠር አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

  • በቀን የሚወስደው የፈሳሽ መጠን ማነስ
  • በቤተሰብ ውስጥ የጠጠር ህመም መኖር
  • አመጋገብ: እንስሳት ተዋፅዖ ፣ ሶዲየም፣ በዝቅተኛ መጠን አትክልት እና ሲትረስ መወሰድ
  • 75 በመቶ የኩላሊት ጠጠርና የ የ 95 በመቶ በፊኛ ውስጥ የሚፈጠሩ ጠጠሮች ወንዶች ላይ የሚፈጠሩ ናቸው። ከ 20-70 የዕድሜ ክልል ያሉ ወንዶች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው።
  • የአልጋ ቁራኛ አልያም እምብዛም የማይንቀሣቀስ ሰው
  • ሞቃታማ በሆነ አካባቢ መኖር
  • ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እንዲሁም፤ የሽንት ፍሰት መዛባት
  • እንደ ታይሮይድ እና ሲስቲንዩሪያ ያሉ ህመሞች
  • ለመሽናት የሚያግዙ መድሀኒቶች እና የጨጓራ አሲድ የሚቀንሱ መድሀኒ ቶች

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

እንደ ጠጠሩ ቦታ መጠንና ቅርፅ የሚለያዩ ቢሆንም ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸዉ፡-

  • በሆድ አካባቢ የሚሰማ ህመም
  • ምንም ምልክት አለመታየት
  • ቶሎ ቶሎ ሽንት መምጣት እና አጠዳፊ የሽንት ፍላጐት መኖር የሽንት ፊኛ ዉስጥ ጠጠር መኖሩን አመላካቾች ናቸዉ።
  • ጠጠር በሽንት ማስወገድ
  • ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ
  • ደም የቀላቀለ ሽንት
  • በሚሸኑ ጊዜ ማመም ወይም ማቃጠል
  • የታቸኛው የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦ ላይ የተቀረቀረ ጠጠር ካለ ሽንት መፍሰስ ከጀመረ በኋላ በድንገት ማቋረጥ ሊኖር ይችላል
  • አንዳንድ ጊዜ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እና የሽንት ቧንቧ መዘጋት ሊያገ ጥምና ቋሚ ወይም ጊዜያዊ የኩላሊት ስራ መዛባት ሊያጋጥም ይችላል

በጠጠር ምክንያት ምን አይነት የሆድ ህመም ሊከሰት ይችላል?

  • የህመሙ ቦታና ክብደት እንደ ቦታው ፣ እንደ አቀማመጡ እና እንደየሰዉ ይለያያል። የጠጠሩ መጠን ከህመሙ መጠን ጋር አይገናኝም። ትንንሽ ሆነው ሻካራ የሆኑ ጠጠሮች ትልልቅ ሆነው ለስላሳ ከሆኑ ጠጠሮች የባሰ ህመም ያስከትላሉ።
  • የጠጠር ህመም ፤በዉል ከማይታወቅ የጎን ህመም እስከ ከባድ የህመም ደረጃ ሊደርስ ይችላል። ህመሙ በአቋቋም ወይም አቀማመጥ እና በእን ቅስቃሴዎች ሁኔታም ሊባባስ ይችላል። ከደቂቃዎች እስከ ሠዓታት የሚዘ ልቅ ህመም ይፈጠርና ከዚያም ህመሙ እየቆየ ጋብ የሚል ይሆናል። ይህ ዓይነት ህመም ከጠጠር ጋር የተያያዘ ምልክት ነው በአብዛኛዉ።
  • ህመሙ ጠጠሩ ባለበት ጎን በብዛት የሚኖር ይሆናል። በአብዛኛው ከእም ብርት በታች ና የጎን ሆድ ወደ መራቢያ አካላት አካባቢ የሚሰራጭ ህመም ከማቅለሽለሽና ማስመለስ ጋር የጠጠር ህመም መለያ ምልክቶች ናቸው።
  • ፊኛ ውስጥ ያለ ጠጠር፤ ከእምብርት በታች ህመም እና ወንዶች ላይ በሽንት አወጋገድ ወቅት፤ ብልት ጫፍ ላይ ህመም ሊፈጥር ይችላል።
  • ጠጠር የሽንት ማስተላለፊያ አካላት ዉስጥ ሲቀር የሚፈጥረው ድንገ ተኛ ህመም ፋታ የሚሰጥ ባለመሆኑ በዚህ ሰዓት ወዲያውኑ ሀኪም ዘንድ መቅረብ ግድ ይሆናል።

የኩላሊት ጠጠር ኩላሊትን ምን ድረስ ይጎዳል?

በኩላሊት ወይም በላይኛው ሽንት ማስተላለፊያ (ዩሬተር) ውስጥ የተቀረቀረ ጠጠር ሽንት እንደልብ እንዳይተላለፍ ያደርጋል። እንደዚህ ያለ የማስተላለፊያ መደፈን ፤ ከኩላሊት ሽንትን ተቀብለው ወደላይኛው ሽንት ማስተላለፊያ (ዩሬተር) የሚወስዱ ትንንሽ ቧንቧዎች በፈሳሽ ብዛት እንዲወጠሩ እና ከጊዜም ብዛት የኩላሊት ስራ መዳከም እንዲመጣ ያደርጋል።

ምርመራዎች፡-

ምርመራዎች የምናካሂደው ጠጠር መኖሩን ለማወቅና ተከትለውት የሚመጡ ውስብሰብ ችግሮች መኖር አለመኖራቸዉን ለመለየት ብቻ ሳይሆን፤ ጠጠሩ እንዲፈጠር ያረጉትን ምክንያቶች ለማወቅም ጭምር ነው።

የራዲዮሎጂ ምርመራዎች፡-

1.   ኬዩቢ አልትራሳውንድ: ይህ ምርመራ በቀላሉ የሚገኝና ብዙ ወጪ የሚያስወጣ ምርመራ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ጠጠር መኖሩንና ተያይዞ የመጣ የሽንት ማስተላለፊያ መዘጋት መኖሩን ለማየት የምንጠቀመው የህክምና ዘዴ ነው።

2.  ኬዩቢ ራጅ: የጠጠሮችን መጠን ቅርፅና ቦታ ለማየት የሚረዳን የምርመራ አይነት ሲሆን ከህክምና በኋላ በተለይ ካልሲየም ጠጠሮች መኖራቸውንና መጠናቸውን ለማየት ያግዛል። ነገር ግን እንደ ዩሪክ አሲድ ያሉ ጠጠሮችን በራጅ ለማየት አስቸጋሪ ነው።

3.  ሲቲ ስካን: ከሁሉም ምርመራ አይነቶች ተመራጭ የሆነው ይህ የምርመራ አይነት ሁሉም አይነት መጠን ያላቸውን ጠጠሮችና የማስተላለፊያ መዘጋት መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ይጠቅማል።

4.  ኢንትራቬነስ ዩሮግራፊ: ይህ ምርመራ የኩላሊት ስራ እና አይነት እንዳለ ማሣየቱ ከሌሎቹ ለየት ያደርገዋል። የላይኛው ሽንት ማስተላለፊያ ቱቦ መለጠጥም በዚህ ምርመራ የሚታይ ይሆናል ነገር ግን ከደም ምርመራ የሚገኝ የክሪያትኒን ውጤት የጭመረ ከሆነ ብዙም ጥቅም አይኖረዉም።

የላቦራቶሪ ምርመራዎች፡-

  1. የሽንት ምርመራ: ይህ ምርመራ ኢንፌክሽን መኖሩን የሽንትን አሲዳማነት ፣ በ24 ሰዓት የሚገኝ የሽንት መጠንን ፣ የካልሲየምን ፣ ፎስፈረስን ፣ ዩሪክ አሲድን፣ ማግኒዚያምን፣ ኦክሳሌትን ፣ ሲትሬትን፣ ሰዲያምን እና ክሪያትኒንን መጠን ለማወቅ ይረዳናል።
  2. የደም ምርመራ: የደም ሴል ቆጠራ (ሲቢሲ) የደም ክሪያትኒን፣ ኤሌክትሮላይት እና የስኳር መጠን። ከነዚህ በተጨማሪ ካልሲየም፣ ፎስፈረስ፣ ዮሪክ አሲድና ፓራታይሮይድ ሆርሞን ምርመራ ሊደረግ ይችላል።
  3. ጠጠሩ ከምን አይነት ውህድ እንደተሰራ ምርመራ ማካሄድ ምን አይነት ህክምና እንደሚደረግ ለማወቅ ይረዳል።

የኩላሊት ጠጠር ህመምን መከላከል

የጠጠር ህመምን እንዴት እንከላከላለን?

የጠጠር ህመም ከ50-70 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ተመልሶ ይፈጠራል። ጥሩ የመከላከያ መንገዶችን መጠቀም ይህንን ዕድል ወደ 10 በመቶ ያክል ወይም ከዛ በታች ዝቅ ያደርገዋል። ስለዚህም ሁሉም ጠጠር ህመም ያለባቸው ሰዎች የሚከተሉትን መከላከያ መንገዶች እንዲከተሉ ይመከራል።

በአጠቃላይ

1. ውሃ አብዝቶ መጠጣት

  • 12-14 ብርጭቆ ወይም 3 ሊትር በላይ ውሃ መጠጣት
  • ውሃው የተገኘበት ቦታ እንደ መጠኑ አስተዋፅዖ የለውም
  • የሚወስዱት ውሃ መጠን በቂ መሆኑን ለማወቅ በቀን ከ2-2.5 ሊትር ሽንት መሽናትዎን ያረጋግጡ
  • ውሃ በዛ ያለው ሽንት ጠጠር እንዳይፈጠር የሚያደርግ ሲሆን በጣም ቢጫ ከሆነ ግን በቂ ውሃ አለመውስድዎን ያመላክታል
  • ከምግብ በኋላ እና ከመተኛትዎ በፊት 2 ብርጭቆ ውሃ ከእንቅልፍ ሲነሱ ደግሞ 1 ብርጭቆ ውሃ መጠጣት ልምድ ያድርጉ፤ ለሊት ለመሽናት ደጋ ግመው የሚነሱ ከሆነ ቀንና ማታ በቂ ውሃ እንደወሰዱ ማመላከቻ ነው።
  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴና አድካሚ ስራ የሚሰሩ ከሆነ በላብ የሚወገደ ውን ውሃ ፈሳሽ በመውሰድ መተካት ተገቢ ነው፤
  • የሩዝ ውሃ እና የፍራፍሬ ጁሶችን በብዛት መውሰድ ለመከላከል ጥሩ መንገድ ነው።
  • ያስታውሱ: ከሚወስዷቸው ፈሳሾች ቢያንስ 50 በመቶ ውሃ መሆኑን ያረጋ ግጡ፤ ከ ፖም ፣ ክራንቤሪ እና ግሬን ፍሩት የሚሰሩ ጭማቂዎች እና ከቸኮ ሌትናስኳር ማጣፈጫዎች እና አልኮል መጠጦች ራስዎን ያርቁ

2. ከጨው መቆጠብ: ጨው በሽንት የሚወደውን የካልሲየም መጠን የመጨመር ተግባር አለው ስለዚህም በቀን ውስጥ ከ 6ግራም የበለጠ ጨው መጠቀም አይመከርም

3. ከእንስሳት ተዋፅዖ መራቅ: እንደ ዶሮስጋ አሣና እንቁላል ያሉ ምግቦች የዩሪክ አሲድ ጠጠሮች እንዲፈጠሩ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ

4. የተመጣጠነ ምግብ: እንደ ሙዝ፣ አናናስ ናብርቱካን ያሉ ፍራፍሬዎች እነ ካሮት እና ቃሪያ ያሉ አትክልቶች እንደገብስ እና አጃ ካሉ ጥሬዎች ጋር መመገብ እንዲሁም የስንዴ ዳቦ፣ ከፓስታና ስኳር መራቅ ተገቢ ነው

5. ቫይታሚን ሲ በቀን ከ 1000 ሚግ በላይ አለመውሰድ፣ ማታ ከባድ ምግብ አለመመገብ እና ውፍረት መቀነስ ሌሎች መንገዶች ናቸው ካልሲየም ጠጠር ለመከላከል፡ ካልሲየም መድሀኒት እና የወተት ተዋፅኦ አለመጠቀም፣ ካልሲየም መድሀኒት መውሰድ አስፈላጊ ከሆነ ከምግብ ጋር መውሰድ፣ ታይዛይድ መድሀኒት ካልሲየም በሽንት እንዳይወጣ በማድረግ ጠጠር እንዳይፈጠር ይከላከላሉ

አክሳሌት ጠጠር ለመከላከል: አረንጓዴ አትክልቶች ፣ ቀይስር እና ስኳር ድንች፣ እንጀራ፣ ፖም ወይን፣ ለውዝ ቃሪያ፣ ማርማላታ ቸኮሌት አኩሪ አተር እና ካካዋ አለመጠቀም

ዩሪክ አሲድ ጠጠር ለመከላከል: አልኮል፣ የእንስሳት ስጋ እና የእንስሳት ተዋፅዖ፣ ምስር፣ ባቄላ፣ እንጉዳይ፣ ቆስጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ አይስክሬምፕ የተጠባበሱ ምግቦችን አለመመገብ፤ ቆሪጥ አሲድን የሚቀንሱ እንደ አሉፒዩሪኖል ያሉ መድሀኒቶችን መጠቀም፤ ፖታሲየም ሲትሬት ሽንትን ቤዛማ ስለሚያደርግ የመከካከል ባህርይ አለው። በተጨማሪ ውፍረትን መቀነስ ሽንት ከመጠን ያለፈ አሲዳማነት እንዳይኖረው ስለማያደርግ ጠቀሜታ ይኖረዋል

ህክምና

ጠጠር የሚታከምበት መንገድ እንደቦታው ፣ መጠኑ ፣ ምልክቶቹና የተሰራበት ውሁድ ይለያያል። በአጠቃላይ ሁለት ዋና ዋና መንገዶት አሉ። እነዚህም ቀዶ ጥገና ሳንጠቀም የምናረገው ህክምና እና በቀዶ ጥገና ናቸው።

1. ቀዶ ጥገና የማያስፈልገው

5 ሚሜ በታች የሆኑ ጠጠሮች ምልክታቸው ከጀመረ ከ 3-6 ሳምንታት በራሳቸው በሽንት ይወገዳሉ። በዚህ ጊዜ ሀኪሙ በዋነኝነት ምልክቶቹ እና ጠጠሮቹ ከታካሚው ያለ ቀዶ ጥገና እንዲወገዱ ማድረግ ይሆናል።

አጣዳፊ ህመም ያለዉ ታካሚ በጡንቻ ወይም በደም ስር የሚሰጥ ማስታገሻ (NSAIDs) ሊያስፈልጉት ይችላል። ቀላል ህመም ከሆነ የሚዋጡ ማስታገሻዎች በቂ ናቸው።

ውሃ አብዝቶ መጠጣት ህመም ሊያባብስ ስለሚችል ሁኔታውን መከታተልና ህመም በማይኖርበት ጊዜ 2 እስከ 3 ሊትር መጠጣት ተገቢነው። ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና ትኩሳት ሲኖር በደም ስር ፍሳሽ መስጠት ያስፈልጋል። ጠጠሩ በተወገዳ ጊዜ እንደ ማጥለያ አይነት ዕቃ በመጠቀም ወስዶ ማስመርመር ያስፈልጋል።

በላይኛው የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦ ውስጥ የሚገኙ ጠጠሮች ከፍተኛ ህመም ሊፈጥሩ ስለሚችሉ፤ ቱቦው እንዳይጨመቅ የሚያደረጉ መድሀኒቶች መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል። ተጓዳኝ ትኩሣት፣ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ ካለ ተገቢ እርምጃ መውሰድ ይገባል።

2. ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው መቼ ነዉ

የህክምና ባለሙያዉ፤ በዋነኝነት አራት የቀዶ ጥገና አይነቶች ሊጠቀም ይችላል። ለታካሚው የሚያስፈልገው የቱ እንደሆነም የሚወሰነው በሀኪሙ አማካኝነት ነው። የቀዶ ጥገና አይነቶቹ ኤክስትራ ኮርፖሪያል ሾክ ዌቭሊቶትሪፕሲ፣ ፐርኩታኒየስ ኔፍሮሊቶትራፕሲ ፣ ዩሬተሮስኮፕና ክፍት ቀዶ ጥገና ናቸው።

ቀዶ ጥገና በቂ ጊዜ ተሰጥቷቸው በራሳቸው ያልተወገዱ ጠጠሮችን 6 ሚሜ በላይ የሆኑ ጠጠሮችን፣ የሽንት ፍሰትን የሚዘጉ ጠጠሮችን እና በተደጋጋሚ ኢንፌክሽን የሚፈጥሩ ጠጢሮችን ለማስወገድ ያስፈልጋል።

የኩላሊት መዳኮም ከታየ አስቸኳይ ቀዶ ጥገና ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል?

. ኤክስትራ ኮርፖሪያል ሾክ ዌቭሊቶትሪፕሲ

ይህ መንገድ መጠናቸው 1.5 ሳሜ በታች የሆኑ ወይም በላይኛው የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦ ያሉ ጠጠሮችን ሰውነት ላይ ምንም አይነት መከፈት ሳይኖር በጣም ብዙ ሞገዶችን ከማሽን በመልቀቅ ብቻ ጠጠሮቹን ወደ ትንንሽ ጠጠሮች በመፈረካከስ በሽንት እንዲወገዱ ለማድረግ የሚረዳ የህክምና ዘዴ ነው። ታካሚው ይህንን መንገድ ከተጠቀመ በኋላ የላይኛው ቱቦ እንዳይዘጋ ከተፈራ ስቴንት ሊደረግለት ይችላል። ከዚህ ህክምና በኋላ ፈሳሽ አብዝቶ መውሰድ ትንንሽ የሆኑት ጠጠሮች እንዲወገዱ ይራዳል። ደም የቀላቀለ ሽንት የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን፣ የጠጠር ጨርሶ አለመፈረካከስና አለመወገድ ፣ የኩላሊት መጎዳትና የደም ግፊት መጨመር ሊያመጣቸው ከሚችላቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች የሚጠቀሱ ሲሆኑ በአጠቃላይ ህክምናው እምብዛም አስጊ አይደለም። ይልቁኑም፤ ሆስፒታል መተኛት፣ ሠመመን እና ሰውነት መክፈት ስለማያስፈልገው እንዲሁም ህመም ብዙም ስለማይፈጥር ለሁሉም ዕድሜ ሠዎች የሚሆን ህክምና ነው።

የሰውነት ክብደታቸው ትልቅ ለሆኑና የጠጠር መጠናቸው 1.5 ሣሜ የሚያልፍ ሰዎች ፣ ነፍሰጡር ሴቶች፣ ኢንፌክሽን የተከሰተባቸዉ ሠዎች፣ የደም ግፊታቸው ከቁጥጥር ዉጪ የሆኑ ሰዎች፣ የመድማት ችግር ያለባቸው ሠዎች እንዲሁም፤ የጠጠሩ ቦታ ወደ ፈኛ የተጠጋና ከፈኛ በታች ለሆኑ ሰዎች የሚመከር መንገድ አይደለም። ህክምናውን ያደረጉ ታካሚዎች ክትትል እና መከላከያ መንገዶችን በሚገባ መተግበር ይጠበቅባቸዋል።

. ፐርኩታኒየስ ኔፍሮሊቶትራፕሲ

ይህን መንገድ ከ1.5 ሣሜ ለሚበልጡና በኩላሊት እንዲሁም በዩሬተር ለሚገኙ ጠጠሮች መጠቀም ይቻላል። የህክምና ባለሙያዎች ብዙዉን ጊዜ ሌሎች የህክምና አማራጮች ዉጤታማ ሳይሆኑ ሲቀሩ የሚወስዱት መንገድ ነው።

በዚህ መንገድ ኣጠቃላይ ማደንዘዣ ከተሰጠ በኋላ ሃኪሙ በተካሚው ጀርባ ላይ ትንሽ ቀዳዳ ካበጀ በኋላ ከቆዳ እስከ ኩላሊት የሚደርስ ቱቦ በአልትራሳውንድ እየታገዘ ይሰራል። ከዚያም ኔፍሮስኮፕ የተባለ ዕቃ አስገብቶ ጠጠሩን ያወጣዋል። ትልልቅ ጠጠሮች ሲሆኑ በድምፅ ሞገዶች ከተፈረካከሡ በኋላ ጠጠሮቹን የማውጣት ስራ ሊሰራ ይችላል። ይሄ ኔፍሮሊቶትሪፕሲ ይባላል።

መድማት፣ ኢንፌክሽን፣ እንደ አንጀት ያሉ ሌሎች የሆድ ዕቃ አካላት መጎዳት፣ የሽንት ከቱቦው ውጪ መፍሰስ ብረት ውስጥ ውሃ መቋጠር ተያይዞው ሊመጡ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል ይጠቀሣሉ።

ሆኖም የሚቀደደው የሰውነት ክፍል በጣም ትንሽ በመሆኑ፣ በአንድ ቀዶ ጥገና ሁሉም ጠጠሮች መውጣት በመቻላቸው እና ረጅም ጊዜ ሆስፒታል የሚያስተኛ ባለመሆኑ ተመራጭ መንገድ ነው።

. ዩሬትሮስኮፕ

በታችኛው 2/3 ዩሬተር የሚገኙ ጠጠሮችን ለማስወገድ ይህ መንገድ ተመራጭ ነው። ማደንዘዣ ከተሰጠ በኋላ ቀጭን ካሜራ ያለው ዩሬተሮስኮፕ የተባለ መሳሪያ በታችኛው የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦ ውስጥ ገብቶ ወደላይኛው ቱቦ (ዩሬተር) ይላካል። ጠጠሩ በካሜራው ከታየ በኋላ እንደመጠኑ ተፈረካክሶ ወይም እንዳለ ይወገዳል። መጠኑ ትንሽ ከሆነ በመያዣ ተይዞ ይወጣል። ትልቅ ከሆነ ደግሞ ወደ ትንንሽ ጠጠሮች ተፈርክሶ በሽንት እንዲያልፉ ይደረጋል። ታካሚው የዛኑ ዕለት ወደ ቤቱ መሄድና ከሁለት ወይም ሶስት ቀናት በኋላ በዕለት ተዕለት ተግባሩን መቀጠል ይችላል።

ያለ ምንም መቀደድ የሚደረግ ህክምና በመሆኑ፣ ለነፍሰጡር ሴቶች፣ ከመጠን ያለፉ ክብደት ላላቸው ሰዎችና የመድማት ችግሮች ላለባቸው ሠዎች ደህንነት አስጊ አለመሆኑ ተመራጭ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ሲጠቀሡ፤ ደም የቀላቀለ ሽንት ፣ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እና የታችኛው የሽንት የማስተላለፊያ ቱቦ ላይ ጠባሳ መጣልና ማጥበብ አሰጊ የሚባሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ናቸው።

. ክፍት ቀዶ ጥገና

ይህ ህክምና የሚያመጣው ህመም ከፍተኛ የሆነና ከ5 እስከ 7 ቀናት ሆስፒታል የሚያቆይ ህክምና ነው። አዳዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ ለዚህ የህክምና መንገድ ያለው ቦታ እየቀነስ መጥቷል፤ ስለዚህም በጣም ውስብስብ ለሆኑ እና ትልልቅ ጠጠሮች በሚገጥሙበት ሁኔታዎች ካልሆነ ብዙም ጥቅም ላይ አይውልም። ዋነኛ ጥቅሙ ብዙ እና ትልልቅ ጠጠሮችን በአንድ ጊዜ ማስወገድ መቻሉ ነው። ለዚህም ከገንዘብ እና ጊዜ አንፃር በተለይ ለታዳጊ አገሮች ጠቃሚ ነው።

የጠጠር ህመም የተከሰተበት ሰዉ መቼ ሐኪም ማማከር አለበት?

  • ፈሳሽና መድሀኒት ሲወስድ ማቅለሽለሽና ማስመለስ ካጋጠመ
  • ሆድ አካባቢ በህመም ማስታገሻ የማይሻሻል ህመም በሚከሰት ጊዜ፤
  • ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ሽንት ሲሸኑ ማቃጠል ከሆድ ላይ ህመም ጋር ተይይዞ ሲታይ፤
  • ደም የቀላቀለ ሽንት ሲስተዋል፤
  • ባጠቃላይ ሽንት አለመሽናት ሲኖር